November 18, 2018

ODF Letter to Ethiopian Religious Organizations

ነሐሴ 2 ቀን 2008 ዓ.ም.

ለተከበሩ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ

ለተከበሩ ሼህ ሙሃመድ አወል ኡመር ጀማል
የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት

ለተከበሩ ሪቨረንድ ዶ/ር ዋቅሥዩም ኢዶሣ
የኢትዮጵያ ኢቫንጀሊካል ቤተክርስቲያን መካነ-ኢየሱስ ፕሬዚዳንት

ለተከበሩ አርክባይሾፕ ካርዲናል ብርሃነእየሱስ ሱራፌል
የኢትዮጵያ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን መሪ

ለተከበሩ ፓስተር ፃዲቁ አብዶ
የኢትዮጵያ ኢቫንጀሊካል ቤተክርስቲያን ፌሎዉሺፕ

ለተከበሩ ዶ/ር ኢያሱ ኤሊያስ
የኢትዮጵያ ቃለ ሕይወት ቤተክርስቲያን ፕሬዚዳንት

አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ
የአክብሮት ሰላምታችንን እያቀረብን በዚህ ደብዳቤ አማካይነት የምናቀርብልዎትን አገራዊ ጉዳይ በጥሞና አይተዉ በሃይማኖት መሪነትዎ የሚጠበቅብዎትን ተገቢ ሚና እንዲጫወቱ በትህትና እንጠየቅዎታለን፡፡

ክቡርነትዎ በቅርብ እንደሚከታተሉት የአገራችን ወቅታዊ ሁኔታ እጅግ አሣሣቢ ወደ ሆነ አቅጣጫ እየሄደ ይገኛል፡፡ በኦሮሚያ ክልል የተቀጣጠለዉ የሕዝብ አመፅ ዘጠነኛ ወሩን ያስቆጠረና እስከአሁንም ተጠናክሮ የቀጠለ ሲሆን ገዢዉ ቡድን እየተጠቀመበት ያለዉ የመሣሪያ ኃይል ሊያቆመዉ የሚችል እንቅስቃሴ አይደለም፡፡ ገዢዉ ቡድን በቅርቡ በጎንደር የተነሣዉን የሕዝብ አመፅም እንደ ኦሮሚያዉ ሁሉ በጉልበት ለማቆም እየሞከረ ነዉ፡፡

የመንግሥትን ሥልጣን በኃይል የተቆጣጠረዉ ቡድን በሕዝቡ ላይ የሚያደርሳቸዉ በደሎችና የሚያደርጋቸዉ አላስፈላጊ ጫናዎች ከመጠን አልፈዉ ያስነሷቸዉን የአመፅና የተቃዉሞ እንቅስቃሴዎች በመሣሪያ ኃይል ብቻ ለዘለቄታዉ ማቆም እንደማይቻል የእስከአሁኖቹ ሂደቶች በቂ ማረጋገጫዎች ናቸዉ፡፡ ገዢዉ ቡድን ግን ከዚህ በመለስ ለመንቀሳቀስ ምንም ዓይነት ፍላጎት ሲያሳይ አይታይም፡፡ ለሕዝቡ ሰላማዊ ተቃዎሞዎችና የመብት ጥያቄዎች ተገቢዉን መልስ መስጠት ካልተቻለ ደግሞ ሁሉም ነገር ከቁጥጥር ዉጭ ሆኖ ማቆሚያ ወደማይገኝለት የእርስ በርስ ግጭትና ደም መፋሰስ ሊያመራ ይችላል የሚል ስጋት አለን፡፡

ስለሆነም የዚያች አገር ጉዳይ ያገባናል የሚሉ ወገኖች ሁሉ በጠረጴዛ ዙሪያ ተሰባስበዉ በአገራችን አጠቃላይ ችግሮች ላይ ጥልቅ ዉይይት ማድረግና የመፍትሔ አቅጣጫዎችን መቀየስ መቻል አማራጭ የማይገኝለትና ለነገ ሊባል የማይገባዉ አንገብጋቢ አገራዊ ጉዳይ እንደሆነ እናምናለን፡፡ በዚህ ረገድ ከአንዳንድ የፖለቲካ ድርጅቶች ጋር የጀመርናቸዉ ጥረቶችና ያደረግናቸዉ ተደጋጋሚ ዉይይቶች ተስፋ ሰጪ ምልክቶችን እያሳዩ ነዉ፡፡ የእርስዎና የሌሎችም የአገራችን ታዋቂ የሃይማኖት መሪዎች ጥረት ቢታከልበት ደግሞ ጅምሮቻችን የምንፈልገዉን ዉጤት ያስገኛሉ ብለን እናምናለን፡፡

ክቡርነትዎ በግልፅ እንደሚረዱት ለበርካታ ዜጎቻችን ሕይወት መጥፋት ምክንያት የሆኑት የአገራችንና የሕዝቦቻችን ዉስበስብ ችግሮች በጥቂት የፖለቲካ ድርጅቶች ጥረት ብቻ መፍትሔ ማግኘት የሚችሉ አይደሉም፡፡ ስለሆነም በሕዝባችን ዘንድ ሰፊ ተቀባይነትና ከበሬታ ያላቸዉ፣ ሁሉንም ወገን በእኩል ዓይን የሚያዩና ለአንድ ወገን ብቻ በማድላት የማይታሙ፣ ከምንም በላይ ደግሞ የሕዝባችንን ችግር በቅርበት የሚከታተሉ የሃይማኖት ተቋማት ተሣትፎ እጅግ አስፈላጊ መሆኑ አጠያያቂ አይደለም፡፡ ይህን ደብዳቤ ለክቡርነትዎ ለመፃፍ ያነሣሣንም ይህ ፅኑ እምነታችን ነዉ፡፡ ስለዚህ እርስዎም ዛሬ አገራችንንና ሕዝባችንን ለገጠሟቸዉ ችግሮች ቅድሚያ በመስጠት ከሌሎች የሃይማኖት ተቋማት መሪዎች ጋር በመተባበር ገዢዉን ቡድን ጨምሮ የዚያች አገር ጉዳይ ያገባናል የሚሉ ድርጅቶች ሁሉ የሚሣተፉበት አገር-አቀፍ ኮንፈረንስ ተዘጋጅቶ የጋራ ዉይይት በማድረግ ዘላቂ መፍትሔ እንዲፈልጉ አገር-አቀፍ ጥሪ እንድታደርጉ በአክብሮት እንጠይቃለን፡፡

ከሰላምታ ጋር

ሌንጮ ለታ
የኦሮሞ ዲሞክራሲያዊ ግንባር ፕሬዚዳንት

ODF Letter to Ethiopian Religious Organizations

Comments are closed.